Thursday, January 11, 2018

የቋራው ካሳ-አንድ ሀገር የመፍጠር ህልምና የሀገር ልማት ረሃብ…

የቋራው ካሳ-አንድ ሀገር የመፍጠር ህልምና የሀገር ልማት ረሃብ፤ | ታላቁን ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ቴዎድሮስን በጥር ወር የመጀመሪያ ሣምንት ለመዘከር ስለ ታላቁ ንጉሥ ትረካውን ቀጥሏል፡፡ አንድ ሀገር የመፍጠር ህልም በሀገር ልማት ርሃብ ላይ ሲል የታላቁን ንጉሥ ገድል ይተርክልናል፡፡ | ሄኖክ ስዩም |
ሁለት ነገር በአንዴ አርግዞ በየቁራጭ ርስቱ እፎይ ካለው መሣፍንት የቀደመ ህልም አለመ፡፡ አንድም ብዙ ሀገር አንድ ስለማድረግ፤ የምን ብዙ ሀገር ብሎ ከታሪክ የሚቃረን ብዙ ሰው ይኖራል፡፡
እውነቱን ግን አንደብቀውም፤ የጠገበ መስፍን ሁሉ ሰፈሩን ሀገር እያለ አንዷን ታላቅ ሀገር ሺ ቦታ በትነዋት የዋሁን ገበሬ ለየቀዬው ጦር ይሰለፍ ዘንድ አበሳውን አሳዩት፡፡ ደግሞም አንድ ሀገር የመመስረቱ ጉዞ የገዛ ቤተሰብ ከንቱ ምኞት ከማፍረስ ጀመረ፡፡
ከአራት መከራክር እስከ በጌምድር፣ ከጃናሞራ እስከ የጁ የነበረው የየራስ ህልም አንድ ህልም ሆነ፡፡ ወዲህ ደግሞ ሌላ ምኞት አለ፡፡ ዘምና የለማች ሀገር መፍጠር፤ ቱርክ በመሳሪያው የማያስፈራራት፤ ግብጥ በጥበቡ እንቅልፍ የማይነሳት፤ አውሮጳ በመላው የማያንበረክካት ሀገር መፍጠር፡፡ መይሳው የወንዜ ሰው አልነበረም፡፡ ስለ ወንዙ ሳይሆን ስለ ሀገሩ የሚጨነቅ መሪ ሆነ፡፡
የተበደሉት ከበቡት፤ የበደሉት ተዋጉት፡፡ ድል ለጭቁኖች እየሄነች የመጨረሻው ጦር ቧሂት ላይ ተፈታ፡፡ ዘር የሚቆጥረው መንፈስ በብርቱ ክንድ ተረታና ደረስጌ ዘውዱን ደፋ፡፡
መይሳው ወንዜ አምላኪ ቢሆን መናገሻው ገለጉ በሆነች፤ ግን መጣ፡፡ ጋፋት መሀል ጥበብን ፍለጋ፤ ደግሞም ወረደ መቅደላ ታላቁን የምኞቱን አምባ ሊገነባ፡፡
Henry Stern taken prisoner by Tewodros II in Abyssinia in 1863 Rev Henry Aaron Stern, 1820 to 1885, British missionary Tewodros II, baptized Theodore II c 1818 to 1868 Emperor of Ethiopia From El Mundo en la Mano published 1875

ራስን ማጥፋት ምን ጀግንነት ነው ቢል የዛሬ ሰው አይገርመኝም፤ ዘመን በቆሙበት የሚመተር እውነት አለው፡፡ ስንቱን ዝም ያሰኘው ጀግና ራሱን ሲያጠፋ ፈሪ ተባለ፡፡ በሞት ስርየት እንዳለ ከነበር እንማራለን፡፡
አቤት ያቺ ገጣሚ “የሸዋንም ንጉሥ ሲንቁ ሲንቁ የትግሬንም ንጉሥ ሲንቁ ሲንቁ……” ወንድ አለራስዎ ገለውም አያውቁ አለች፡፡
ታሪክ የጀግንነትን ልክ በሞቱ ለምን ለካው? እንደተወለደ ራሱን ያጠፋ ሰው እኮ አልነበረም፡፡ አይሻል ላይ ድል አጣጥሟል፤ ማን ነክቶኝ ባዩን ራስ አሊን እያሳደደ፡፡
ጉራምባስ የማን ክንድ ታይቶ፤ ግብጥን ከአይማ ወንዝ እስከ ካርቱም ማን አሳደዳት? ደጃች ውቤን ማን ማረከ? በጦር ሜዳ ውሎ ማሸነፍን ለማያውቅ ራስ መግደል ፍርሐት ይሆናል፡፡
ሁሉን አሸንፎ ራስን ስለ ሀገር ክብር አሳልፎ መስጠት ግን የጥቂቶች ናት፡፡ ጥር ነው፡፡ እኒህ ታላቅ ንጉሥ የተወለዱበት ወር፡፡ ገና የምንትዋብ ፍቅር የጀግነነት መንገድ ሲሆን እናያለን፡፡ የጎንደሩን የቁንጅና ውድድር እናነሳለን፡፡ ህልምህን አሳየን ብለን ምኞቱን እመኛለን፡፡ ይቀጥላል…

No comments:

Post a Comment