ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም የጥር ወርን መጀመሪያ ለታላቁ ንጉሥ ለንጉሠ ነገሥት ዐፄ ቴዎድሮስ እንስጠው ብሎ ጀግናውን መተረክ ጀምሯል፡፡ ቋረኛው አንበሳ የጀግንነት ልኩ ሲል የተወለደባትን ስፍራ የማስታወሻው መጀመሪያ አድርጓታል፡፡ | ሄኖክ ስዩም በድሬ ቲዩብ
አንዷን ኢትዮጵያ ሰላሳ አርባና ሀምሳ ቦታ ቦጫጭቀው ለዕለት ደስታቸው የሚኖሩ መሳፍንት በበዙበት ዘመን አንድ ሰው ተወለደ፡፡
የዚህን ጀግና እትብት የቀረበረች ቋራ እንደምን የታደለች ናት፡፡ ቋራ ከዚያም ቀድሞ የጀግኖች ከዚያም በኋላ የጀግኖች ምድር ናት፡፡
የጥር ወርን በራፍ ታላቁን ምድር እያነሳን እንዘክረዋለን፡፡
ቋራና እንደክብሩ ከስሙ አስቀድሞ ለመጠራት የመጀመሪያው ሰው መይሳው አልነበረም፤ ለምሳሌ በጎንደር ዘመን የነበሩት የእቴጌ ምንትዋብ ልጅ ቋረኛው ኢያሱ በሚል ይጠሩ ነበር፡፡
ራሳቸው እኒያ ብርሃን ሞገሳ የተባሉት ብርቱ ሴት የጎንደር ዘመን የፖለቲካ እቴጌም ቋረኛ ናቸው፡፡ በሱሲኒዮስና በሰርጸ ድንግል ዜና መዕዋሎች የቋራን ወንድ የጦር ሜዳ ውሎ ማየት ይቻላል፡፡
ቋራ በርሃ ነው፤ ግን ደግሞ ደን የተጠቀጠቀበት፤ የዓይማ ወንዝ በረከት ያረሰረሰው፤ አባታቸው ሐይሉ ወልደጊዮርጊስ የቋራ ተወላጅ እና ስም ያላቸው ጀግና ነበሩ፡፡ እናታቸው ደግሞ የእንፍራንዟ አትጠገብ ናቸው፡፡ አትጠገብ የደንቢያ ባላባት ልጅ ናቸው፡፡
መይሳው በልጅነታቸው ፊደል የቆጠሩት ሥርዓት የተማሩት ማህበረ ስላሴ ገዳም ነው፡፡ ለዚህ ነው አረብኛ ቋንቋ እንጂ ሃይማኖት እንዳልሆነ የገባቸው፡፡
ማህበረ ሥላሴ በቋራ ምድር የሚገኝ በአብርሐ ወ አጽበሐ የተተከለ የታላላቅ ቅዱሳን አድራሻ ነው፡፡ ገዳሙ ድንበር ላይ ነው የሚገኘው፤ ድንበር ጥሶ ስለሚገባ ጠላት መይሳው ፊደል በሚማሩበት የልጅነት እድሜ የሀገር ዳር ድንበር ጉዳይንም አብረው እያጠኑ አደጉ፡፡
ዛሬ ገደባችሁ ብላ ጠዋት ማታ የምትዝተው ግብጽ የመይሳው ካሳ የልጅነት ቃታ መለማመጃ የጀግንነት ልኩን መስፈሪያ ነበረች፡፡
በወጣትነቱ የተሳተፈባቸው ውጊያዎች ግብጽ በሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ስትዘልቅ ሱዳን ድረስ ገብቶ አደብ ያስገዛት የነበረው ታሪክ ሺ ቦታ ተቆራርጣ የየመሳፍንቱ የአንገት ጌጥ በሆነችው ኢትዮጵያ ከዳር ዳር ናኘ፤ ይህንን ለመሰለ ጀግና ልጅን ቀድሞ መዳር የቀደመችዋ ኢትዮጵያ መሪዎች የፖለቲካ ዘዴ ነውና፤ እቴጌ መነን የልጅ ልጃቸውን ለወጣቱ ጀግና ለመዳር ልጃቸውን ራስ አሊን አሳመኑ፤ ቋራ የበጌምድር አማች ሆነ፡፡
የደሃ ደካማ የለውም የተባለው መይሳውም እንደተባለው በረታ፤ ምንትዋብን ካገባ በኋላ በዋለበት የጦር ሜዳ ሁሉ ድል ለእሱ ሆነች፡፡
ከእግዜር በታች የተባሉ መሳፍንት እያንዳንዱ ቀን እግሩ ስር የሚወድቁበት ክፍ ቀን ሆነ፡፡ ብዙ ቦታ ለብዙ እኔ ባይ መሳፍንት የሆነችዋ ሀገር ዳግም መልካም ቀን መጣላት፡፡
በጌ ምድር ከራስ ጉግሳ አንደርታ ከራስ ወልደ ጊዮርጊስ ጎን ቆም የአንድ ሀገር ልጅ ሁለት ጎራ የሚዋደቅበትን የታሪክ ቁስል የሚጠግን የብርሃን ጭላንጭል ታየ፡፡
ከጉራምባ እስከ መከሁ ለፍልሚያ የወጣው መይሳው ማታ ድሉን ማጣጣም ጀመረ፡፡
ይህ ጀግና ለኢትዮጵያ የተሰጣት ጥር ስድስት ቀን 1811 ዓ.ም. ነበር፡፡ ከአማቾቹ አንድ ሙከት የተነሳው ጀግና ኢትዮጵያን ታህል ታላቅ ሀገር እጁ ገባች፤ ጥርን ለመታሰቢያነቱ ሰጥተንዋልና ቀጥለናል፡፡